አመታዊውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ዘንድሮም በደማቅ ሁኔታ ለአምስተኛ ጊዜ ማክበር ተጀምሯል። የዘንድሮን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት የኢፌዲሪ ሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን ”ራስን መቻል ለዘላቂ ሰላም እና ለአካታች ልማት” በሚል መሪ ቃል በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተር ለ3 ተክታታይ ቀናቶች ይከናወናል።
በዝግጅቱ ከባለፈው አመት በተሸለ ከ115 በላይ ድርጅቶች ስራዎቻቸውን በኤግዝቢሽን ለህዝብ ይፋ ከማድረግ አልፎ፣ የልማት አጋሮች፣ የግሉ ዘርፍ፣ የመንግስት ተቋማት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላቶችን የሚያሳትፉ 7 የፓናል ውይይት መድረኮች ይከናወናሉ።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ “መንግሥት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው.” ብለዋል።
በመክፈቻ ንግግራቸው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝደንት አቶ አህመድ ሁሴን “ድርጅቶች የመደራጀት መብታቸውን በመጠቀም በልማት፣ በዴሞክራሲ እና በሰላም ግንባታ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው” ብለዋል።
በቀጣዮቹ ሁለት ቀናቶች (የካቲት 27 እና የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም.) በፓናል ውይይቶቹ የሚነሱ ርዕሰ ሃሳቦች በሰላም ግንባታ እና በመልካም አስተዳደር፣ በዲጂታል ሚዲያ፣ በስርዓተ ጾታ፣ በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃ፣ በሰብአዊ ድጋፍ እንዲሁም ጠቅላላ ምርጫ እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና ላይ ውይይቶች ይደረጋሉ።
የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርዓያሥላሴ ``ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት በቅንጅት እና በመናበብ መሥራት የሁሉም ድርሻ ነው`` ብለዋል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን ቢራቱ ``ሳምንቱ በባለድርሻ አካላት መካከል ጠንካራ ትስስር እና የልምድ ልውውጥ እንዲኖር ግብዓት እየኾነ መምጣቱን ገልጸዋል።”
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ዋነኛ አላማ በዘርፉ ያሉ ድርጅቶች በማህበረሰቡ ውስጥ በሚደረጉ ማናቸውም እንቅስቃሴ ያላቸውን ሚና ለህዝብ እና ለባለድርሻ አካላት እንዲያስተዋውቁ ዕድሉን መፍጠር እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከመንግስት፣ ከግሉ ዘርፍ እና ከሌሎች የልማት አጋሮች ጋር ተቀራርበው በትስስር የሚሰሩበትን መድረክን ማመቻቸት ነው።
በዘንድሮው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች 115 የሲቪል ማህበረአሰብ ድርጅቶች ስራቸውን ለህዝብ የሚያሳዩበት ይህ አመታዊ መርሃ ግብር የዘርፉን የገጽታ ግንባታ እንቅስቃሴ የበለጠ ከማጉላቱ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጾ ይኖረዋል፡፡





. 


